
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ ሕዝብ ምክር ቤትና የብሔረሰቦች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡


ርዕሰ መስተዳድሩ በመክፈቻ ንግግራቸው የክልሉን መንግስት የ2018 ዋና ዋና የልማት ዕቅድና የትኩረት አቅጣጫዎች በመዳሰስ ላይ ሲሆኑ፤ በንግግራቸው በትኩረት ካነሱዋቸው ነጥቦች ሰላምና ፀጥታ ዋነኛው ነው፡፡
ያለፈው 2017 በክልሉ በብዙ መልኩ የስኬት አመት ነበር ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በሁሉም የልማት አውታሮች የሀገራችን የማንሰራራት ማሳያ የሚሆን ውጤት ማስመዝገብ ከመቻሉም በላይ ለጠንካራ ተቋማዊ የአሰራር ዝርጋታና ለተቋም ግንባታ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት አመርቂ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡



ለዚህ ስኬት መብቃት የተቻለው የልማቶች ሁሉ ቁልፍ እና የደምስር ለሆነው የሰላም ግንባታ ስራ ልዩ ትኩረት በመስጠት ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት ባደረገ መልኩ በተሰራ አድማሰ ሰፋፊ ውጤታማ የሰላም ግንባታ ስራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ሰላም የክልሉ መለያና አርማ የማድረጉ ስራ በ2018 የበጀት ዓመትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያስታወቁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን በክልሉ ባሉ ድልብ የባህል ዕሴቶች የመፍታት ልምድ ለማዳበር በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም በላይ የላቀ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትንና ትብብርን በማረጋገጥ የተረጋጋ ሰላምና ጸጥታ ለማሰፈን ከአጎራባች ሀገራት፤ ከክልሎች እንዲሁም በዞኖች መካከል የሰላምና ፀጥታ የጋራ ፎረሞችን በመፍጠር ጭምር ለውጤታማ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ስራዎች ትኩረት የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።




