የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት በ32ኛ መደበኛ ስብሰባው የክልሉ መንግስት የ2019 በጀት 85.8 ቢሊዮን እንዲሆን ውሳኔ አሳለፈ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በክልሉ መንግስት የ2019 በጀት አመት የበጀት ዕቅድ ላይ በዝርዝር በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል፡፡

መስተዳድር ምክር ቤቱ በዚሁ ስብሰባው የክልሉን መንግስት የ2019 በጀት ዓመት የበጀት ዕቅድ፡-

በክልሉ መሪ የልማት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችን ከማስፈፀም፤ ለክልሉ ሕዝቦች በጋራ የመልማት ትልም ስኬት በሁሉም ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ እንዲሁም ሀገራዊ እና ክልላዊ የዘላቂ ሰላምና የሁለንተናዊ ብልፅግና ራዕይ ዕውን ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶችንና የልማት ኢኒሼቲቮች ትግበራን ከማጠናከር አኳያ በማጠን በዝርዝር ተወያይቷል፡፡

በዚህም ምክር ቤቱ የክልሉን መንግስት የ2019 በጀት፡- የመደበኛ ወጪዎች፣ የካፒታል ወጪዎች እንዲሁም ለዞኖች የሚሰጥ የድጎማ በጀት ጨምሮ በጠቅላላው 85,774,012,025 (ሰማንያ አምስት ቢሊዮን ሰባት መቶ ሰባ አራት ሚሊዮን አስራሁት ሺህ 25 ብር) እንዲሆን በሙሉ ድምፅ በመወሰን ለክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት እንዲተላለፍ መርቷል።    

ከበጀት አመቱ አጠቃላይ በጀት ውስጥ፡- ሃምሳ ስድስት ነጥብ ሁለት  በመቶው (56.2%) በውስጥ ገቢ የሚሸፈን መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ ቀሪው አርባ ሶስት ነጥብ ስምንት በመቶ (43.8%) በፌዴራል መንግስት ድጎማ የሚሸፈን መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ የውስጥ አቅምን በማጎልበት በራስ አቅም የህዝብ አዳጊ የልማት ጥያቄዎችን በብቃት ለመመለስ መስራት በቀጣይም የክልሉ መንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ለዚህም በ2019 የበጀት ዓመት በክልሉ በሁሉም የአስተዳደር ዕርከኖች አላስፈላጊ ወጪዎችን መቀነስ እና በየደረጃው ለገቢ አሰባሰብ ስራ ልዩ ትኩረት በመስጠት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሃዊ ገቢን በተቀናጀ አግባብ በመሰብሰብ የውስጥ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ክልሉ በርካታ ፀጋዎች አሉት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በየአካባቢው በግብርና፤ በኢንዱስትሪ፤ በቱሪዝም፤ በማዕድን እና በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ያሉ እምቅ አቅሞችን ተጠቅሞ ከየዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በመስራት የገቢ ምንጮችን ማስፋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ 

በተጨማሪ የተመደበው በጀት ለልማት ስራዎች እንዲውል  ማድረግ እንዲሁም የህብረተሰብ ተሳትፎ በማጠናከር በመደጋገፍ የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።

Leave a Reply