ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የክልሉ መንግስት ከ361 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በዘፍኔ ከተማ ያስገነባቸውን የንፁህ የመጠጥ ውሃ እና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መርቀው አገልግሎት አስጀመሩ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ በጋሞ ዞን፤ ቦረዳ ወረዳ ይፋዊ የስራ ቆይታ በማድረግ የተለያዩ የልማት ስራዎች ጉብኝት ደረጉ ሲሆን፤ የተለያዩ የተጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶችንም መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል፡፡

ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚሁ የስራ ቆይታ በቦረዳ ወረዳ ዘፍኔ ከተማ ሲደርሱ፤ በዞኑ እና በወረዳ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፤ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም በዘፍኔ ከተማ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ የስራ ቆይታቸው በተለይ የክልሉ መንግስት ከ361 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በወረዳው፤ በዘፍኔ ከተማ ያስገነባቸውን የዘፍኔ ከተማ የንፁሁ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት እንዲሁም የዘፍኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በይፋ መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል።

በምረቃ ስነስርዓቱ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤  በዛሬው ዕለት የቦረዳ ወረዳ ህዝብ የዘመናት ጥያቄ የነበሩት የንፁሁ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም በቅርበት ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል የህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋም (ሆስፒታል) ምላሽ በማግኘቱ የተሰማቸውን ልዩ ደስታ ገልፀዋል።

የክልሉ መንግስት ለማህበራዊ ብልፅግና ትልም ስኬት የመሠረታዊ አገልገሎቶች ተደራሽነትን ለማሳደግ በትኩረት በመስራት ላይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይ ከመሠረታዊ ፍላጎቶች እጅግ አስፈላጊ የሆኑት ፍትሃዊ የጤና እና የንፁሁ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትን በማሳደግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በክልሉ ለማህበራዊ ዘርፍ ልማት እና ለሰው ተኮር ተግባራት ቅድሚያ በመስጠት በመደረግ ላይ ባለው ርብርብ የዘፍኔ ከተማ የንፁሁ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም የዘፍኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት መጀመር መቻላቸውንም ገልፀዋል።

የክልሉ መንግስት በጤናው ዘርፍ ለጤና አገልግሎት ጥራት፤ ፍትሀዊነትና ተደራሽነት ልዩ ትኩረት በመስጠት ዘርፈ ብዙ ውጤታማ ስራዎችን መስራት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

በተለይ በጤና ተቋማት ግንባታ፤ በጤና መድህን እንዲሁም በሕብረተሰብ ጤና አገልግሎት በተከናወኑ በርካታ  ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉንም አብራርተዋል።

በክልሉ ጥራት ያለው ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ በመደረግ ላይ ካለው ጥረት ባለፈ፤ ከፌዴራል መንግስት እና ከአጋር አካላት ጋር ትብብሮችን በማጠናከር እንደ ሀገር ለተያዘው የማይበገር የጤና ሥርዓት ግንባታ ግብ ስኬት በትኩረት በመሰራት ላይ ስለመሆኑም ገልፀዋል፡፡

የዘፍኔ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በክልሉ መንግስት ከ210 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሆስፒታሉ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ለከተማው ህብረተሰብና ለአካባቢው ነዋሪዎች ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት በቅርበት ተደራሽ ለማድረግ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በተጨማሪም የክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በአንድ ወረዳ አንድ የማህበረሰብ ፋርማሲ ኢኒሼቲቭ አካል የሆነው የማህበረሰብ ፋርማሲ በወረዳው፤ በጋጋ በጎቾ ቀበሌ ተመርቆ በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በተመሳሳይ መንግስት ከመሠረታዊ ፍላጎቶች እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ፍትሃዊ የንፁሁ የመጠጥ ውሃ ሽፋንና ተደራሽነትን በማሳደግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት በመስራት ላይ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ 

በዚህ ረገድ በክልሉ በዘንድሮ የ2018 በጀት ዓመት ያለፉ አሥር ወራት ብቻ በከተማና በገጠር 65 የውሃ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ421 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡ 

በዛሬው ዕለት የተመረቀው የዘፍኔ ከተማ የንፁሁ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ከ157 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ከ34 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ተናግረዋል።

ውሃ ህይወት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በከፍተኛ ወጪ የተገነባውን የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ጠብቆ ተንከባክቦ በማቆየት ህብረተሰቡን በታለመው ልክ በአግባቡ ማገልገል እንዲችል መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በዘላቂነት ውሃ ለማግኝት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ስራዎችን አጠናክሮ ተፈጥሮን መንከባከብ እንደሚገባ የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የአካባቢው ህብረተሰብ አረንጓዴ አሻራን ባህል በማድረግ ዛፍ የመትከልና ተፈጥሮን የመጠበቅ ስራዎችን በዘላቂነት እንዲያከናውን አሳስበዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በቀጣይም መሠረታዊ የሆነውን ፍትሃዊ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን በማሳደግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፌዴራል መንግስት፤ በየደረጃው ካሉ መዋቅሮች እና ሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በትኩረት የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ካለ ልማት ይኖራል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ህዝቡ ኅብረት እና አንድነቱን አጠናክሮ ሙሉ ትኩረቱን ወደ ልማት በማዞር ቦረዳን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም ህዝቡ ግንቦት 24 በሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በነቂስ በመሳተፍ እና ሁለንተናዊ ብልፅግናዋ የተረጋገጠ የተሻለች ተምሳሌት ሀገር ለትውልድ ለማሻገር በመትጋት ላይ የሚገኘውን ብልፅግና ፓርቲን በመምረጥ የተጀመረውን ልማት እንዲያስቀጥል ጥሪ በማቅረብ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።  

Leave a Reply